Skip to main content

በክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና በፕላንና ልማት ቢሮ የተካሄደ የውሀ ተቋማት ቆጠራ ግኝቶችና ውጤቶች ላይ የጋራ ውይይት ተካሄደ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ በ2017 ዓ.ም የተካሄደው የውሀ ተቋማት ቆጠራ ግኝቶችና ውጤቶች ላይ የሁለቱ ቢሮዎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በተገኙበት በሆሳዕና ከተማ የጋራ ውይይት አካሄደዋል ።

የክልሉ ውሀ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ የክልሉን የመጠጥ ውሃ ሽፋንን አስመልክቶ በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በፍትሀዊነት ተደራሽ ለማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረተ የተደራጀ የውሃ ተቋማት ቆጠራ መካሄዱን ገልፀው በቆጠራው ግኝትና ውጤት መሰረት ክልላዊ የውሀ ሽፋኑን በማደራጀት ወደ ትግበራ ለመግባት መድረኩ መመቻቸቱን ተናግረዋል ።

የቆጠራውን ውጤት ተከትሎ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን እና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በውሀ ተቋሟት አስተዳደር ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ዳዊት ገልፀዋል ።

የተካሄደው የውሀ ቆጠራ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳዊት  የውሀ ሽፋንና የብልሽት ምጣኔው ከፕሮጀክሽን ከተገኘው ውጤት ይልቅ ሁለቱም ተቋማት ካካሄዱት የቆጠራ ውጤቶች ላይ ተመስርቶ ማደራጀት እንደሚገባና የቆጠራው  የመጨረሻ ውጤት ከቢሮዎቹ በተወጣጡ ኮሚቴዎች በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ተጣርቶና ተደራጅቶ ሊቀርብ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የልማት መረጃና ስነ ህዝብ ጉዳዮች ዘርፍ ሃላፊ ዶ/ር ፈለቀች ተክለማሪያም በበኩላቸው ከመረጃ ጥራትና አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለመፍታት እንደክልል ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የተካሄደው ቆጠራ ውጤት በፕሮጀክሽንና በጥናቱ መካከል ያለውን የሽፋን ልዩነት ክፍተት እንደሚፈታ ገልፀዋል።

የተካሄደው የቆጠራ ውጤት መቀራረቡ እንደ ክልል የተደራጀ መረጃ ለማግኘት እንደሚያግዝ ገልጸው ባጠረ ጊዜ ተገቢው ማስተካከያ ተደርጎ ሊቀርብ ይገባል ብለዋል ።

በቢሮ ኅላፊ ማዕረግ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የመጠጥ ውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር በክልሉ የመጠጥ ውኃ ሽፋንን ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የውሀ ተቋማት ቆጠራ ግኝት ውጤቱ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ትክክለኛ መረጃ መነሻነት እንደሚያገለግል ተናግረዋል ።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት በክልሉ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በማቺንግ ፈንድ የሚቀርቡ ድጋፎች ላይ ከበጀት አመዳደብ ጀምሮ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።

በተያያዘም በየተካሄደው የውሀ ተቋሟት ቆጠራ ግኝቶች ተቀራራቢ ከመሆናቸው አኳያ ልዩነቶችን በማጥበብ ሰነዱን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ በማድረግ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ለመድረኩ የተዘጋጀ የውሀ ተቋማት ቆጠራ ግኝት ሰነዶችን በየደረጃው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።

Image