Skip to main content

በወራቤ ከተማ ገርማማ ቀበሌ በበጎ አድራጊ ግለሰብ ከ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የየንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።

ግንቦት 10/2018

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ አስተዳደር ገርማማ ቀበሌ በበጎ አድራጊ ሀጂ ፈድሉ ሱልጣንና ቤተሰቦቻቸው የተገነባ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካን በቢሮ ኅላፊ ማዕረግ የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የውሃ ፕሮጀክቱ በሶላር የሀይል አማራጭ የሚሰራና ከ4 ሺህ በላይ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም ያለው መሆኑ በምረቃ ወቅት ተገልጿል።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ዘይኔ ቢልካ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የዞኑ ህዝብ ግምባር ቀደም ጥያቄ መሆኑን በማስታወስ የዞኑ መንግስት ችግሩን ለመፍታት በተለያዩ አማራጮች ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

በጎ አድራጊ አካላት የዞኑን የውሃ ችግሮች በመፍታት በኩል የድርሻቸውን እያበረከቱ መሆኑን በማስታወስ የገርማማ ፕሮጀክትን እውን ላደረጉት ሀጂ ፈድሉ ሱልጣንና ቤተሰቦቻቸው ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በዞኑ በሁሉም አከባቢዎች በርካታ የንጹህ ውሃ አማራጮችና ምንጮች ቢኖሩም የአቅርቦት ፍላጎቱን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን አቶ ዘይኔ ተናግረው የውሃ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ባለሃብቶች የድርሻቸውን በማበርከት ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ያሲን ከሊል በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በኩል የከተማዋን ህዝብ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን ለማሻሻል በስፋት እየተሰራ መሆኑን አስታውሰዋል።

በሀጂ ፈድሉ ሱልጣን የተገነባው የገርማማ ውሃ ፕሮጀክት የቀበሌውን የውሃ ችግር በማስታገስ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው በመግለጽ ባለሃብቱንና ቤተሰቦቻቸውን አመስግነዋል።

በአለም ባንክ ፈንድ በገርማማ ቀበሌ እየተገነባ ያለውና በርካታ የከተማዋን ክፍሎች ተደራሽ የሚያደርገው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን አቶ ያሲን ገልጸው ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማዋን ሽፋን በእጅጉ እንደሚያሻሽለው አብራርተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ አስተያየታቸውን ያከፈሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከአመታት እንግልት እንደታደጋቸው ተናግረው እንደ መብራት አቅርቦት ያሉ ቀሪ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱላቸው ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ የገርማማ አከባቢ ማህበረሰብ ለሀጂ ፈድሉ ሱልጣንና ቤተሰቦቻቸው የክብር ስጦታ አበርክተው ዝግጅቱ ተጠናቋል።

የዞኑ የመንግስት ኮምኒኬሽን ዘግቧል ።

See less

Image