በዋን ዋሽ ፕሮግራም ከ115 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ
ግንቦት 26/2018(ወልቂጤ)
ቢሮው በቀጣይ በክልሉ በዋን ዋሽ (One wash) ፕሮግራም ለሚያስገንባቸው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከኮንተራክተሮች ጋር በወልቂጤ ከተማ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ ዋን ዋሽ ፕሮግራም ትልቁ ተልዕኮው በውሃ፣ ጤናና ትምህርት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀው ለማህበረሰቡ የጤና መሠረት እንዲሁም የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል ።
ዋን ዋሽ(One wase) በቀድሞ ደቡብ ክልል እና በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጨምሮ ለበርካታ አመታት የቆየ ፕሮጀክት ሲሆን በገጠር አካባቢ ለሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ትልቅ እገዛና እፎይታ በመስጠት በርካታ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ሲሉ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።
አቶ ዳዊት አክለውም ዋን ዋሽ ፕሮግራም በማጠናቀቂያና በተጨማሪ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚገኝና በዚህ ማጠናቀቂያ ወቅት ላይ 4 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለማከናወን የውል ስምምነት መገባቱን ተናግረው በዚህም ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በክልሉ ሳጃ ከተማ ፣አበጀ ፣ ጨቦና ኮምበል የሚገነቡት እነዚህ የንጹህ መጠጥ የውሃ ፕሮጀክቶች ከ1 መቶ 15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደርግባቸው መሆኑንና ከ58 ሺ ህዝብ በላይ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ገልጿል።
አሁን ካለው አለም አቀፍና ሃገር አቀፍ የነዳጅ እጥረት ምክንያት ለተቋራጮች የስራ እክል እንዳይሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
የሚገነቡት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶቹ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ክፍል ላይ ለውጥ የሚያመጡ መሆኑን በመገንዘብ ግንባታዎቹ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአስተዳደር ሃላፊዎችና የህብረተሰ ክፍሎች ትብብር እንዲያደርግ አቶ ዳዊት ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚናዳብ ኮንስትራክሽንና ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ኪዳኔ እና የቢንያም ሻምበል ህንፃና ውሃ ስራዎች ተቋራጭ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ሻምበል በበኩላቸው
አስፈላጊውን የሰው ሃይልና ማሽን በሟሟላት ፕሮጀክቶቹን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ማስፋፋት ላይ የህብረተሰቡና የዘርፉ አመራሮች ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ትብብራቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 