በማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል በ2018 በጀት ዓመት በውሃ፣ መስኖ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለጸ።
ነሐሴ 7/2018 የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና ተጠሪ ተቋማቱ በ2018 በጀት ዓመት በውሃ፣ መስኖ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገለጹ።
ቢሮው የተቋማቱን የ2018 በጀት አመት የሥራ አፈጻጸም የሚገመግምና የ2019 በጀት አመት ዕቅድ የፈጻሚዎች ዝግጅት መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ፤ በ2018 በጀት ዓመት የተመዘገቡት ውጤቶች ከዕቅድ አፈጻጸም ባሻገር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ስኬቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዳዊት አክለውም እነዚህ አበራች ውጤቶች ሊመዘገቡ የቻሉት በተቋማት መካከል በተፈጠረ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር፣ የባለድርሻ አካላት ትብብርና የተቀናጀ ጥረት መሆኑን ጠቅሰው፤ የተገኙ ስኬቶች ለ2019 የበጀት ዓመት ዕቅዶች ስኬታማነት ጥሩ መነሻ እንደሚሆኑ አስገንዝበዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የቀረበው የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ዘርፍ 207 ተቋማት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ በዚህም 619 ሺ ህበላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በመስኖ ዘርፍ 2 ሺህ 975 ሄክታር መሬት ለማልማትና 5 ሺህ 950 አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ የሁለት ከፍተኛ የመስኖ ግድቦች የጥናትና ዲዛይን ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተመላክቷል።
በማዕድን ዘርፍ 809 ባህላዊና 20 አነስተኛ ደረጃ በድምሩ 829 የማዕድን ማምረቻ ፈቃዶች የተሰጡ ሲሆን፣ ለ9 ሺህ 698 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በተጨማሪም ከዘርፉ ከ256 ሚሊዮን 397 ሺህ ብር በላይ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን፣ 13 ሚሊዮን 110 ሺህ 871 ሜትር ኪዩብ የኮንስትራክሽን ማዕድን ምርት መመዝገቡ ተገልጻል።
በኢነርጂ ዘርፍም 72 ሺህ 614 የሶላር መሣሪያዎች ተሰራጭተው ከ363 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፣ ከ82 ሺህ በላይ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና በርካታ ባዮጋዞች ተገንብተው ወደ ሥራ በመግባታቸው ገደማ 89 ሺህ 901 ቶን የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት እንዳይለቀቅ ማድረግ ተችሏል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በመድረኩ ማጠቃለያ ንግግራቸው፤ ተሳታፊዎች በ2019 የበጀት ዓመት ግቦች ላይ ሙሉ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፣ ለቀጣይ ሥራዎች ትኩረት የሚሹ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ነባር የንጹህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶችን በልዩ ትኩረት ማጠናቀቅ፣ የፈጻሚዎችን የመፈጸም አቅም በተዋረድ ማሳደግ፣ በየዘርፉ የሚደረጉ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጠናከር፣ በማዕድን ዘርፍ የአሌንታ ጥናት ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥና አሠራር ላይ ተጠያቂነትንና ግልጸኝነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ ዳዊት አሳስበዋል።
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን መኔዶ፤ ከቢሮ ኃላፊው ጋር በመሩበት ወቅት በማዕድን ዘርፉ በፈቃድ አሰጣጥ፣ በማዕድን ምርትና በገቢ አሰባሰብ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ መኮንን አክለውም በቀጣይ በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ጥልቀት ያለው ድጋፍና ክትትልን ማጠናከር እንዲሁም ለውሳኔ አሰጣጥ የሚረዱ የመረጃ አደረጃጀትና አያያዝ ሥርዓቶችን ማዘመን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ የክልሉ የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በበኩላቸው፣ በመስኖ ዘርፍ የተጠናቀቁ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎችን በመነሻነት በመጠቀም ቀጣይ የመስኖ ልማት ሥራዎችን ማጠናከር፣ የመስኖ ተጠቃሚነትን ማሳደግና የተገኙ ውጤቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ተጠሪ ተቋማት በ2019 በጀት ዓመት የተያዙ እቅዶችን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በቁርጠኝነትና በተጠያቂነት ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የክልሉ መንግስት ኮምኒኬሽን
See less
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 