በውሃ፣ በመስኖና በማዕድን ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ሥራዎች መሠራታቸው ተገለጸ።
ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም. (ወልቂጤ)
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና ተጠሪ ተቋማቱ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን የሚገመግም እና የ2019 በጀት ዓመት የፈጻሚዎች ዝግጅት መድረክ በወልቂጤ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በ2018 በጀት ዓመት በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን፣ በአማራጭ ኃይል፣ በማዕድን ልማት እና በመስኖ አውታር ጥናትና ግንባታ ዘርፎች በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በውሃ በመስኖና በማዕድን ዘርፍ ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዩ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የመስኖ ተቋማት ቆጠራ መካሄዱንና በተመሳሳይ የውሃ ተቋማት ቆጠራ በማካሄድ ከሽፋንና ከተቋማት አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አቶ ዳዊት ገልጸዋል።
የቢሮውን የውስጥ አቅም ለማሳደግ የላብራቶሪ ቁሳቁሶችን የማሟላትና በጥልቅ ጉድጓዶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በተገቢው ለመለየት የሚያግዙ የቦርሆል ካሜራ ቴክኖሎጂዎችን የማሟላት ሥራዎችም መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በመስኖ ዘርፍ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት የመስኖ አውታር ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ሥራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።
በማዕድን ዘርፍ የኮንስትራክሽንና የኢንዱስትሪ ማዕድናትን በማምረት ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን፣ በኃይል ዘርፍም በሶላርና በባዮጋዝ ቴክኖሎጂዎች አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዳዊት የተመዘገቡት ውጤቶች የመላው የሴክተሩ ሠራተኞች ትጋትና ጥረት ውጤት መሆኑን ጠቁመው፣ ሠራተኞች ለሴክተሩ ስኬትና ለተልዕኮው ውጤታማነት ያበረከቱትን ሚና አድንቀዋል።
ኃላፊው በ2019 በጀት ዓመት ባለፈው ዓመት በተመዘገበው ውጤት ሳይረኩ የህዝቡን የልማትና የዕድገት ፍላጎት ለማሟላት የበለጠ ትጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ለዚህም የመንግሥትን አቅም በመጠቀም፣ ከረጂና አጋር አካላት፣ ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከግል ባለሀብቶችና ከህዝቡ ጋር በመተባበር የተቀመጡ ዕቅዶችን በተግባር ማሳካት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በመድረኩ የቢሮውና የተጠሪ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም፣ የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ እየቀረቡ ይገኛል።
መድረኩ በቀጣይ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በዝርዝር በመገምገም፣ በ2019 በጀት ዓመት የሚከናወኑ የሥራ ዕቅዶችን በማጠናከርና በጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ እና ከተጠሪ ተቋማትና ከቢሮው ምክትል የዘርፍ ሃላፊዎች የግብ ስምምነት ፊርማ ስነስርአት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
See less
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 