Skip to main content

የቆዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለፀ።

ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም (ወልቂጤ)

በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ ሀንገዳ ቀበሌ በክልሉ መንግሥት ካፒታል በጀት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የሀንገዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ፕሮጀክቱ 12 የውሃ ቦኖዎችን፣ 193 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ፣ 100 ኪዩቢክ ሜትር የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን፣ 3.1 ኪሎ ሜትር የግፊት መስመር እና 8.4 ኪሎ ሜትር የማሰራጫ መስመር ያካተተ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያገለግላል።

በፕሮጀክቱ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ፣ የቆዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ክልሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ክልሉ ከአዲስ አደረጃጀት በኋላ ለሀንገዳ የውሃ ፕሮጀክት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ዶክተር መሀመድ፣ በቀጣይም የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተጨማሪ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ በበኩላቸው፣ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ በውሃ ዘርፍ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸው፣ የሀንገዳ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚህ ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ዳዊት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ላደረጉ አካላት በራሳቸውና በተቋማቸው ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የህብረተሰቡን የጤናና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ ህብረተሰቡ የተገነባውን የውሃ መሠረተ ልማት በአግባቡ በመጠቀምና በመጠበቅ ዘላቂነቱን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ፣ በዞኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ እንዲያገኙ ከክልሉ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ነዋሪዎች ቀደም ሲል ንጹህ ውሃ ለማግኘት ረጅም ርቀት በመጓዝ ብዙ ጊዜና ጉልበት ያጠፉ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን በአካባቢያቸው ውሃ ማግኘታቸው ትልቅ እፎይታ መሆኑን ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ያገኙትን ጊዜ በቤተሰብ፣ በትምህርትና በሌሎች ምርታማ ሥራዎች ላይ ለማዋል እንደሚችሉ ጠቁመው፣ የውሃ መሠረተ ልማቱን በአግባቡ በመጠቀምና በመጠበቅ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ተሳትፎአቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ገጠር ልማት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በክብርት ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ እና አቶ መዘረዲን ሁሰን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የመሠረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ የቢሮው ምክትል የስራ ሃላፍፊዎች፣ የቢሮው ማናጅመንት አባላት ፣ የዞን፣ የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የክልሉ መንግስት ኮምኒኬሽን

See less

Image