አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባሻገር ነባር ፕሮጀክቶች የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባሻገር ነባር ፕሮጀክቶች የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ተጠቆመ። የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የግማሽ አመት አፈጻጸሙን በቡታጅራ ገምግሟል። (ሆሳዕና፣ የካቲት 28/2017)፣ በየአመቱ አዳዲስ የውሃ ፕሮጀክቶችን በእቅድ ደረጃ ከመያዝና ከመገንባት ባሻገር ነባር ፕሮጀክቶች የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡበትን መንገድ መፍጠርና ውጤታማነታቸውን ማጎልበት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ የ2017 በጀት አመት ያለፉትን ስድስት ወራት አፈጻጸሙን በቡታጅራ ከተማ ገምግሟል። በዚሁ ወቅት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ሙሀመድ ኑርዬ (ዶ/ር) እንዳሉት አቅምንና የአካባቢን ፖቴንሺያል መሰረት ባደረገ መልኩ የአዳዲስ ፕሮጀክቶች ግንባታ ግብን ከማስቀመጥ ባሻገር በርካታ የሀገር ሀብት የፈሰሰባቸው ነባር የንጹህ መጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክቶች የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡና የህዝቡን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ማድረግ ይገባል። በተለይም ወቅታዊ ክትትልና ጥገና በማድረግ የውጤታማነታቸውን ዘላቂነት ማጎልበትና የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ዶ/ር ሙሀመድ ተናግረዋል ። ለዚህ ስኬት ደግሞ የውሃ ተቋማት አስተዳደር ፣ ሙያዊ ክትትልና ወቅታዊ ጥገና ስርኣትን ማጎልበቱ ወሳኝ እንደሆነ አብራርተዋል ። ዘርፉ ለግንባታ ፕሮጀክቶች ጥራትና የግንባታ ጊዜ ማስጠበቅ ላይ ብዙ እንደሚጠበቅበት ያነሱ ዶ/ር ሙሀመድ በተለይ የመስኖ ተቋማት እንደ ሀገር ከተያዘው የምርትና ምርታማነት እድገት የሚቆራኙ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይሻሉ ብለዋል። ሴክተሩ በማዕድን ዘርፍ የገቢ አቅምን በማሳደግ፣ የፖቴንሺያል አማራጮችን በማስፋትና የአማራጭ ኢነርጂ አቅርቦትን ማጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል ።እነዚህን ተልዕኮዎች ለማሳካት በየደረጃው ቅንጅታዊ አሰራርንና የመረጃ አያያዝ ስርኣትን ማጎልበት አለበት ብለዋል። የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሃይሉ በበኩላቸው ሴክተሩ በበጀት አመቱ የግብ ስምምነቶችን ፈጽሞ እነዚህን ግቦች ለማሳካት በተደራጀ መንገድ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል ። በተለይም ደግሞ የክልሉን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ በልየ ትኩረት መንቀሳቀሱን ያነሱት አቶ ዳዊት የመስኖ አውታር ልማት ስራን በማጎልበት ዘርፉ በምርትና ምርታማነት እድገት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል ። ከዚህ መነሻም ነባር የመጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅና በአዲስ መልክ የተጀመሩትን ጥራትና የግንባታ ጊዜያቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲገነባ በየደረጃው በእቅድ የተመራ እንቅስቃሴ ተደርጓል ብለዋል። በሌላ በኩልም በማዕድን ልማት ዘርፍ የአለኝታ ጥናቶችን ለማስፋት፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጎልበትና በስራ እድል ፈጠራ ረገድ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግ ላይ ክልሉ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል ። በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ ሃይል ቆጣቢና እንግልትን በሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱንም አስረድተዋል ። ሴክተሩ በቀጣይ በመጀመሪያው ግማሽ አመቱ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ጉድለቶችን በማረም የህዝብን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማስፋት እንደሚኖርበት ገልጸዋል ። የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት በውሃ ተቋማት አካባቢ የሚታየው የሃይል አቅርቦት ችግር ፣ የፕሮጀክቶች ለአመታት መጓተት፣በተሟላ መልኩ አገልግሎት አለመስጠት፣ በጥቃቅን ጉድለቶች ወደ አገልግሎት አለመግባት፣ ለነባር ፕሮጀክቶች የሚሰጠው ትኩረት አናሳነትና የተቋማት አስተዳደር ስርኣት ክፍተት ችግሮች ልዩ ትኩረት የሚሹ ናቸው ብለዋል። ከመድረኩ በየዘርፉ ለተነሱ ጥያቄዎች የቢሮው ምክትልና የየዘርፉ ሃላፊዎችና የተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በግምገማ መድረኩ ማጠቃለያ ላይ ለዋን ዋሸ ምዕራፍ ሁለት ተጠቃሚ 21 የክልሉ ወረዳዎች ከ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ኮምፒውተሮች ድጋፍ ተደርጓል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 