Skip to main content

የኢትዮጵያ ዜጎች የአንድነት ውቅር ፈጥረው በመስራት የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ድህነትን ታሪክ በማድረግ የአድዋ ድል መድገም እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች የአንድነት ውቅር ፈጥረው በመስራት የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ድህነትን ታሪክ በማድረግ የአድዋ ድል መድገም እንዳለባቸው ተጠቆመ፡፡

የካቲት 20/2017(ወልቂጤ)

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ክላስተር መስሪያ ቤቶች "አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ቃል 129ኛው የአድዋ ድል በዓል በጋራ አክብረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ዘር፣ ቀለምና ሀይማኖት ሳይበግራቸው የአላማ አንድነት በመፍጠር በወቅቱ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው ወራሪው የጣሊያን ጦር አድዋ ላይ ድል ካደረጉ እነሆ 129 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል በዘንድሮው ዓመትም ለ129ኛ ጊዜ እየተከበረ ሲሆን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ ክላስተር ሴክተር መስሪያ ቤቶችም "አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል " በሚል መሪ ቃል በጋራ አክብረውታል፡፡በዓሉ በተከበረበት ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንዳሉት የአድዋ ድል ለዓለም ህዝብ ትልቅ አበርክቶ ነው፡፡ታድያ ለድሉ ውጤት መምጣት የዓላማ አንድነት ስለነበር ነው ያሉት ሀላፊው የኢትዮጵያ ዜጎችም የአንድነት ውቅራቸው በማጠናከር የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ባለፈ ድህነትን ታሪክ በማድረግ የአድዋ ድል መድገም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡አባቶች በአስቸጋሪ ጊዜ መስዋእትነት ከፍለው ሀገር አስረክበውናል፤ ይህም ዕዳ ነው በማለት በተለይ መሪን በመከተልና በመደገፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና በማረጋገጥ ዕዳውን መክፈል ከዚህ ትውልድ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በበኩላቸው የአድዋ ድል ውጤት ዋጋ ሳይከፈል እንደማይመጣ ያስተምራል ብለዋል፡፡በመሆኑም ሁሉም በየተሰማራበት የስራ መስክ ብልሹ አሰራሮችን በመዋጋትና ጠንክሮ በመስራት የኢትዮጵያን ልዕልና ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

እምቢ ለባርነት በማለት ከ4ቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተውጣጡ ጀግና ኢትጵየዊያን የ5 ወራት ጊዜን የፈጀ ከ1 ሺ 66 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር በመጓዝ አድዋ ላይ ድል በመቀዳጀት ለዓለም ነፃነትን አስተምረዋል ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵየ ክልል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል ዘርፍ ሀላፊ አቶ ፋሲካ ጌታቸው ናቸው፡፡ይህም ለሀገር መስዋዕትነት መክፈል እንደሚስፈልግም ገልፀው የአሁኑ ትውልድም ድሉን በማልማት ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የበዓሉ ተሳታፊዎችም ጀግንነት እያወሩና እያከበሩ መኖር በቂ ባለመሆኑ በተለይም የአስተሳሰብና የአመለካከት ብሎም የሀይማኖት ልዩነት በመቻቻል መንግስትን በመደገፍ የሀገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ ተገቢ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

Image