የውሃ ብክለትንና ብክነትን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለፀ።
የማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል የውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ከክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በውሃ አካላት ብክለት፣ ብክነትና በውሃ የመጠቀም ፈቃድ አሰጣጥና ትግበራ ፖሊሲ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
መጋቢት 13/2017 ሀላባ ቲቪ
---------------------------
በመድረኩ ላይ በሁለቱም ቢሮ በኩል የተዘጋጁ ለውይይት የሚሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫና የስልጠና ሰነዶች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡትየማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል የውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ በቢሮ ሀላፊ ማዕረግ የውሃ ሀብት ጥናትና አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ሀላፊ ወ/ሮ አለይካ ሹክር ውሃ ለህይወታችን ዋስትና የሆነ ትልቅ ሀብታችን ነው ብለዋል።ስለሆነም የውሃ ብክለትንና ብክነትን ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።በዚሁም መሠረት ከተለያዩ ተቋማትና ፋብሪካዎች ወደወንዝ የሚለቀቁ የውሃ በካዮችን መቆጣጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።ውሃ አልምቶ በማሸግ ስራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ከሚፈለገው መጠንና ጥራት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ውሃ የማቅረብ ሀላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።ተቀራርበን ከሰራን የከርሰ ምድርንና የገፀምድር ውሃ አቅሞች ማሳደግ እንችላለን ሲሉም ተናግረዋል።
ለህዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ የውሃ ተቋማትም ለብርካዎች አካባቢ ተገቢውን ጥበቃ በማድረግ ከብክለት መታደግ አለባቸው ብለዋል።የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ አብረሃም መጫ በበኩላቸው ብክለትንና ብክነትን ለመቅረፍ የተፈጥሮ ሀብትን ማልማት፣መጠበቅና መቆጣጠር እንዲሁም ስለፋይዳቸው የሚዲያ ሽፋን በመስጠትና ለብክለት በሚዳርጉት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል።በዚህም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል።ከሁሉም የብክለት ዓይነቶች የአፈር፣ የውሃና አየር ብክለት በእጅጉ ህዝቡን የሚጎዱ የብክለት ዓይነቶች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።በመሆኑም የውሃና ውሃ አካላት ብክነትን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የዞንና የሰባቱም ክላስተር ከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ስራ አስኪያጆች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት መምሪያና ጽ/ቤቶች ሀላፊዎች፣ የሁሉም መዋቅር ውሃና ማዕድን መምሪያና ጽ/ቤት ሀላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 