Skip to main content

በወልቂጤ ከተማ በመጠጥ ውሀ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ።

ከፌደራል ውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር  እና ከኢትዮጵያ ከተሞች ውሀና ሳኒቴሽን ፌደሬሽን ከተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ በከተማውና አካባቢው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የውሀ ምንጮች የሚገኙበት ደረጃ ከውሀ ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ ከክልሉ ፣ ከዞንና ከከተማው ውሀ ተቋማት የተወጣጡ አካላት ምልከታ በማድረግ አማራጭ ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በመድረኩ እንደተናገሩት ህዳር 2018 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ ለሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል ተሳታፊው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዳይገጥመው የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጀት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል ።

የከተማውን ህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦ ተደራሽነት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ዳዊት አብራርተዋል።

በከተማውና አካባቢው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የቦዠቧርን ምንጭ የማምረት አቅም ማሳደግ፣ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎታቸው የተቋረጡ ነባር ጥልቅ ጉድጓድ የመጠገን  እና አዲስ ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ የማስቆፈር ስራ ይሰራል ብለዋል ።

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የውሀ ኢነርጂ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ከተሞች ውሀና ሳኒቴሽን ፌዴሬሽን ከፍተኛ ድርሻውን የሚወስዱ ሆኖ የክልል የዞን ፣ የከተማውና ሚመለከታቸው አካላት የየራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ዳዊት ተናግረዋል ።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸው በከተማዋ የተፈጠረውን የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የውሀ ኢነርጂ ሚኒስቴርና የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ በመቀናጀት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ለከተማውና አካባቢው ማህበረሰብ ንፁህ የመጠጥ ውሃን  ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት  የሚኒስቴር  መስሪያ ቤቱና የክልል ውሃና መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ።

Image