Skip to main content

በ2017 ከተመዘገበው በላቀ በ2018 እንደሚሰራ የቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ገለፁ ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ፣ የመስኖ ተቋማት አስተዳደር ኤጀንሲና የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ በ2017 በጀት ዓመት የማጠቃለያ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የቢሮ፣ የኤጀንሲ ኃላፊዎች እና የሴክተር ማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ተገመገመ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በውይይት መድረኩ እንደገለፁት በቢሮውና ተጠሪ ተቋሟት በ2017 በጀት ዓመት የተጣሉ ግቦችን ለማሳካት በክልሉ መንግስት፣ በረጂ ድርጅቶችና በህብረተሰብ ተሳትፎ ድጋፍ በመጠጥ ውሀ፣ በመስኖ፣ በማዕድንና በኢነርጂ ዘርፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች መከናወናቹውን ገልፀው በ2018 በጀት ዓመት የተለጠጠ እቅድ በማዘጋጀት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ተናግረዋል ።

በ2017 በጀት ዓመት ለ278 አዲስና ነባር ባለሙያዎች፣ ለ146 ድርጅቶች በውሀ ሀብት የመጠቀም ፣ ፈቃድና ብቃት የማረጋገጥ ስራ መከናወኑ ተገልፆኣል።

በገጠር 408 እና  በከተሞች 5 የመጠጥ ውሃ ጥናት ዲዛይንና ስራ በማከናውን ወደ ትግበራ የተገባ ስለመሆኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ቀርበዋል።

4482 ቀላል ፣ መካከለኛና ከባድ ብልሽት ያለባቸውን ውሀ ተቋማት በመለየት ጥገናዎች የተከናወኑ መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በአጠቃላይ በክልል ደረጃ 120 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ280 ሺ በላይ ህብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በሪፖርቱ ቀርቧል ።

በመስኖ ዘርፍ 1676 አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ ሚያደርግ 8 የመስኖ መልሶ ግንባታ፣ 4082 ሄክታር በማልማት 14744 አባወራና እማወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ጥናትና ዲዛይን ስራ ተከናውኗል።

በበጀት አመቱ በተከናወኑ የመስኖ ስራዎች ከ5000 በላይ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል ።

በማዕድን 177 ኪ.ሜ የአለኝታ ጥናት መጠናቀቁን፣ በክልሉ 7 አይነት ማዕድናትን መለየታቸውና ጥናቱ እንደሚቀጥል፣ 190 ሶላር ፓምፕ ሚያለሙ ጉድጓዶች ጥናትና ዲዛይን ስራዎች መከናወኑን አመላክተዋል።

በምርመራ ፈቃድ 6፣ በባህላዊና በአነስተኛ ለማምረት ለ682 አካላት ፈቃድ መሰጠቱን ከስልሳ ስድስት ሺ በላይ የሶላር ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማሰራጨት 334000 ሕዝብ ተጠቃሚ ሲሆኑ በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፍ የክልሉ ገቢ አቅም ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ መሆኑ ተመላክቷል ።

በውይይቱ የተገኙ የክልሉ ማዕድን ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ማኔዶ እንደገለፁት ተቋሙ የጀመራቸውን የማዕድን ጥናት ስራዎች በሚመለከታቸው አካላት ከተደገፈ የክልሉን አቅምና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንደሚጨምር ገልፀው የውስጥ አቅምን ማጠናከር ይገባል ብለዋል ።

በተያያዘ የክልሉ መስኖ ተቋማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ካሳዬ ተክሌ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ፣ የውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ እና ኤጀንሲው ባደረጉት ቅንጅታዊ አሰራር በአዲሱ በጀት ዓመት ተመርቀው ወደ ስራ የሚገቡ በርካታ የመስኖ ስራዎች እንዳሉ አንስተዋል ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት በቢሮውና ተጠሪ ተቋሟት ደረጃ ያለው አፈፃፀምና ዕቅድ ላይ የተነሱ ጥንካሬዎችና ጉድለቶች በሰራተኛ ደረጃ በጥልቀት ተገምግሞ የስራ ተነሳሽነቱን መጨመር ይገባል ብለዋል ።

በ2018 በየዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን የማሳደግ ፣ በየደረጃው የሚገኙ የቅየሳ መሳሪያዎችን በአግባቡ የመጠቀም ፣ የውሀና የመስኖ ተቋማት ማስተዳደር አቅምን በማሳደግ የህብረተሰቡን ዘለቄታዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ሥራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የማዕድን አለኝታ ጥናትን የሚመለከታቸው አካላት በማሳተፍ የማሳደግ ፣ ነባርና ያልተጠናቀቁ የውሀና የመስኖ ፕሮጀክቶች ባጠረ ጊዜ የማጠናቀቅ፣ አግልግሎት መስጠት ያቆሙ ተቋማት ፈትሾ ወደ ስራ ማስገባት፣ ታዳሽ ሀይል በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ፣ ጨረታዎችና የየዘርፉ አገልግሎቶች በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት እንዲሳለጡ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

Image