በክልሉ በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ (GCF) የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ምልከታ እየተካሄደ ነው
መስከረም 19/2018 (ወልቂጤ)፣
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ (GCF) የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አፈፃፀም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ምልከታ እያደረጉ ይገኛሉ ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ ፕሮግራሙ በክልሉ በሁለት ዞኖችና በአንድ ልዩ ወረዳ በንፁህ መጠጥ ውሃ ፣በመስኖ እና በአካባቢ ጥበቃና በተፋሰስ ልማት ላይ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ በነባሩ ደቡብ ክልል የተጀመረ በበርካታ ውጣ ውረዶች ያለፈ በጠንካራ አመራር ለውጤት የበቃ መሆኑን ገልጸዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መፍታት የህብረተሰቡን በርካታ ማህበራዊ ችግር መፍታት ነው ያሉት ሀላፊ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሻሻልና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ እያደገ የመጣውን የህዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ዳዊት ከፍሎራይድ ነፃ የሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቢሮ ሀላፊ ማዕረግ የቢሮው ምክትልና የውሃ ሀብት ጥናት አስተዳደር ሀላፊ ወይዘሮ አለይካ ሽኩር እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በክልሉ ለበረሃማ መስፋፋት የማይበገር የአረንጓዴ አሻራ ላይ ጠንካራ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ምልከታ የተካሄደበት በሀላባ ዞን የዌራ ዲጆ ወረዳ ቁልቢ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በክልሉ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በ72 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባና ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጋላጭነት የሚቀንስ ስራ በፕሮግራሙ መከናወኑን ተናግረው ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑ የውሃ ተቋማትን ህብረተሰቡ በተገቢው ማስተዳደር እንደሚገባው አሳስበዋል።
በቀጣይ በከንባታ ዞን በሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ የሶዲቾ እና በማረቆ ልዩ ወረዳ የሰሜን ቆሼ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ምልከታ የሚካሄድባቸው መሆኑ ተገልጿል ።
በመስክ ምልከታው የክልል ቢሮ ሀላፊዎች፣ የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ልክነሽ ስርገማ፣ የቢሮው ምክትል ሃላፊዎች ፣ ጨምሮ የተቋራጭ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 