Skip to main content

መሁሉም ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት በማዘመን ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ፣ከብልሹ አሰራር የጸዳ እና እና በእርካታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን መስራት ይገባል :-ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተመርቆ ስራ ጀመረ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) እንደገለጹት በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ከብልሹ አሰራር የጸዳ፣የህብረተሰቡን እርካታ ያረጋገጠ እንዲሁም የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገንብቶ ስራ የጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ አገልግሎት መለየት፣ ማኑዋል ማዘጋጀት፣ቢሮን መገንባትና ማደስ፣ሰራተኛ መረጣ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦት ስራ ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል።

በክልሉ በዛሬው እለት ከተመረቀው ፕሮጀክት ልምድ በመውሰድ በወራቤ፣በቡታጅራ፣በወልቂጤ፣በሳጃ፣በዱራሜ፣በቁሊቶ ከተሞች በ2018 ማጠቃለያ ላይ ሰባት መሶብ የአንድ ማዕከላት እንደሚኖሩ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ተገንብቶ ወደ ተግባር እንዲገባ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮች ለፌደራል እና ለክልል ተቋማት ርዕሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።

በ2018 በጀት አመት በሀገሪቱ እና በክልሉ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ  አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የተንዛዛ፣ የግልጸኝነት ጉድለት ያለው ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ እንግልት የበዛበት እና ተገልጋይ ተኮር ያለመሆኑ በመንግስት እና በፓርቲ ከግንዛቤ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው  ክፍተት በህዝብ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ስለመስተዋሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በሁሉም ዘርፍ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር ) አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እውን ማድረግ መቻሉን አቶ አንተነህ ጠቁመዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለዜጎች የተደራጀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

በክልሉ በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ኮሚቴ በማቋቋም ለስራው ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን አስችሎታል ሲሉም አቶ አንተነህ ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የፌደራል እና የክልል ተቋማትን አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችላቸው የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተገልጋዮችን እንግልት እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ አሰራሮችን የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በሰባት የፌደራል እና የክልል ተቋማት 20 አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም አቶ አንተነህ በንግግራቸው አመላክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሮጀክቶች አስተባባሪ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ብርሀኑ ተስፋዬ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገንብቶ ለውጤት እንዲበቃ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተልዕኮ ከማሳካት አንጻር በሀገሪቱ ሰባት ማዕከላት ለምረቃ መብቃታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ ስድስት ማዕከላት እየተመረቁ ነው ብለዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሀገሪቱ የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽነትና ግልጸኝነትን ከማሳደግ አንጻር ወደ አንድ ደረጃ እንደሚያሳድገውም አብራርተዋል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ፣በቱሪዝም መዳረሻ ልማት፣በከተማ እና በገጠር ኮሪደር፣በአረንጓዴ አሻራ፣በሌማት ትሩፋት፣በስንዴ ልማት እንዲሁም የማዕድን ልማት የኢትዮጵያ ማንሰራራት መገለጫዎች ናቸው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

በመርሐ ግብሩ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የክልሉ መንግስት ኮምኒኬሽን

Image