የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደርገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ጥቅምት 08/2018 (ወልቂጤ)
ቢሮው "የትምህርት ስብራትን ለመጠገን አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ" በሚል መርህ በቀቤና ልዩ ወረዳ ፣ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና በአበሽጌ ወረዳ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደተናገሩ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስተራችን ሀሳብ አመጪነት የተጀመሩ ሰው ተኮር የበጎ አድራጎት ተግባራትን በክልላችንም ይበልጥ አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራዎች መሰረት ቢሮው ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል ።
እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካማዎችንና አረጋዊያን ቤተሰቦችን መደገፍ አንዱ መሆኑን በማመላከት ይህም በመተባበር መስራት እንደሚቻል ዕድልን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በዚህ መነሻነትም ቢሮው በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በአበሽጌ ወረዳ ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን በመጥቀስ ተግባሩ ስኬታማ እንዲሆን ላስተባበሩ አካላት ምስጋናቸውን ችረዋል።
ሀገርን ለመለወጥ የትምህርት ዘርፍን ቅድሚያ ሰጥቶ መደገፍ ወሳኝ መሆኑን ነው አቶ ዳዊት ያስረዱት።
የትምህርት ዘርፍ መጠናከር ሀገሪቱ ወደ አዲስ የስልጣኔ ማማ ለመድረስ ለምታደረገው ጉዞ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለፅ ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎች በርትተው ትምህርታቸውን በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረጉም በተጓዳኝ ወላጆችንም እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት።
ስለሆነም ቢሮው መሰል ድጋፎች አቅም በፈቀደ መጠን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው ለዘርፉ ውጤታማነትም ሁሉም ማገዝ እንዳለበት ሀላፊው አቶ ዳዊት ሀይሉ አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትልና የውሃ አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር በበኩላቸው በክላስተሩ ማህበራዊ ሃላፊነትን ለመወጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍም ለታለመለት ዓላማ እንዲውል መከታተል እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
የወልቂጤ ክላስተር የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ የፖለቲካ አደረጃጀት ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ ገነት ታደሰ ድጋፉ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረው ክንፉ መሰል ድጋፎች በባለፈው ዓመትም ሲያደርግ መቆየቱንና በተለይም በትምህርት ላይ የሚሰራ ስራ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
በቀጣይም መሰል ድጋፎች በሌሎች ዘርፎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማስገንዘብ ለተማሪዎቹ በቀጣይ የተጠናከረ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የተማሪ ወላጆች በሰጡት አስተያየት ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረጉ መደሰታቸውን በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተማሪዎችም ከዚህ ቀደም በትምህርት ቁሳቁስ እጦት ምክንያት ችግር ይገጥማቸው እንደነበር አውስተው ዛሬ የደብተር፣ እስክርቢቶና የቦርሳ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ በትምህርታቸው ጠንክው በመስራት ለተሻለ ውጤት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
በቢሮው የንፁህ ውሃ ሴቶች ክንፍ አደረጃጀት ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን አንጀሎ እንደተናገሩት ቢሮው ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ለእያንዳንዱ ተማሪ የዩኒፎርም ማሰፊያ ገንዘብ፣ ደብተር ስክብሪቶና ደብተር ድጋፍ መደረጉን ተናግረው ክንፉ የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ከቢሮው ጋር በመነጋገር የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል ።
በመድረኩ ላይ የቢሮው አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የወልቂጤ ክላስተር የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አመራር አባላት፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ ከቀቤና ልዩ ወረዳ እና ከአበሽጌ ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም ድጋፍ የተደረገላቸው ወላጆችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 