Skip to main content

በስልጤ ዞን በዳሎቻ ወረዳ በአጋም ሶጃቴ ቀበሌ ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በዳይሬክት ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተመረቀ ።

ህዳር 21/2018 (ወልቂጤ)
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የተገኙት የክልሉ ውሀ ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ እንደተናገሩት 
የዳይሬክት ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅት በክልላችን በተወሰኑ አካባቢዎች የጀመራቸውን የንፁህ መጠጥ ውሀ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በስፋት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቃው ፕሮጀክት የአካባቢውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የፈታ በመሆኑ በዘላቂነት የውሀ ተቋሙን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ እና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ፕሮጀክቱ በፀሐይ ኃይል አቅርቦት የሚሠራና ባለሦስት የውሀ ማጠራቀሚያ ሮቶ ያለው በመሆኑ በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን ለማስተናገድ የሚችልና በዘላቂነት አገልግሎት የሚሰጥ ፕሮጀክት መሆኑ ተመላክተዋል።

ኃላፊው አያይዘው የውኃ ችግር መፍታት ከጤና ጋር የሚያያዝ ዘርፈ ብዙ ችግር መፍታት የሚቻልበት እንደሆነም በአብነት አውስተዋል።

ለፕሮጀክቱ መሳካት የበኩለቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱ ለዳይሬክት ኤድ፣ ለዞን አስተዳደርና ባለድርሻ አካላት የቢሮው ኃላፊ ምስጋና አቅርበዋል።

የስልጤ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው እንደ ዞን የውሃ ሽፋን ከ34 በመቶ ያላለፈ መሆኑን በመጥቀስ ሽፋኑን ለማሳደግ ከክልልና ከአጋር ድርጅቶች በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

ዋና አስተዳዳሪው አያይዘው በዞኑ ለረጅም ግዜ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የውኃ ፕሮጀክቶችን ደረጃ በደረጃ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ።

አቶ ዘይኔ አክለው ፕሮጀክቱ አበርክቶው የላቀ መሆኑን በመግለጽ ማህበረሰቡ ፕሮጀክቱን በመንከባከብ ፣በመጠበቅና በኃላፊነት ስሜት መገልገል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሬድዋን መሶሮ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የክልል ፣ የዞንና የወረዳ ሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ።

Image