በክልሉ በላይኛው ብላቴ ተፋሰስ አካባቢ ለሚካሄድ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታ ጥናት ጉድጓድ ቁፋሮ በስልጤ ዞን ሶስት ቦታ/ሳይት ርክክብ ተካሄደ ።
ህዳር 22/2018 (ወልቂጤ)
የውሀ ኢነርጂ ሚኒስቴር ለከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ልየታ ጥናት ጉድጓድ ቁፋሮ በላይኛው ብላቴ ተፋሰስ በሚገኙ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል በገባው ውል ስምምነት መሠረት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን በዳሎቻ ፣ በሳንኩራ እና በውልባረግ ሶስት ቦታዎች/ሳይት ርክክብ ተካሄዷል ።
በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት በቢሮ ኅላፊ ማዕረግ የክልሉ ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የውሀ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር እንደተናገሩት በክልሉ የላይኛው ብላቴ ተፋሰስ አካባቢ በሚል በተለዩ አራት ዞኖች ላይ ለከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለኝታ ጥናት የሚቆፈሩ ጉድጓዶች በተሟላ መንገድ ተፈፃሚ ለማድረግ ቢሮው ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት ተገቢውን ዝግጅት ማደረጉን ገልፀዋል ።
በክልሉ 9 የከርሰ ምድር የውሃ ጥናት ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ በስልጤ፣ በሀዲያ ፣ በሀላባና በከምባታ ዞኖች ጥናት በተካሄደባቸው በተመረጡ አካባቢዎች የጥልቅ ጉድጓድ ውኃ ቁፋሮ እንደሚካሄድ የገለፁት ወ/ሮ አለይካ እያንዳንዱ ጉድጓድ እስከ 500 ሜትር ጥልቀት ያለው በመሆኑ በጥራትም ሆነ በመጠን የተሻለ ውሀ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል በሚል ተናግረዋል ።
የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮው በተያዘለት ጊዜ ሲጠናቀቅ በመንግስትና በማህበረቡ የሚያጋጥሙ ጫናዎችን ከማስቀረቱ ባሻገር የውሀ ግኝቱን ተከትሎ ቀጣይ ተግባራትን ለማስቀጠልና በፌደራል ደረጃ ክልሉ ተጨማሪ እድሎችን እንዲያገኝና የአካባቢውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
የስልጤ ዞን ውሀ ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ጨፋ ከድር በበኩላቸው ከጥናት ስራ ጀምሮ እስከ ጉድጋድ ቁፋሮ የሚኖረውን ሂደት በተሳካ መንገድ እንዲሳለጥ ከወረዳ እስከ ቀበሌ ካሉ መዋቅሮች ጋር በመነጋገር ተገቢ ዝግጅቶች መደረጉን ገልፀው የወቅቱ የአየር ንብረት ምቹ በመሆኑ የጉድጓድ ቁፋሮ ስራው ከወዲሁ ሊጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የዳር ኮርመር ኮንሰልታንት ሪፕሬዘንታቲቭ የሆኑት አቶ ገለቱ በላይ በበኩላቸው መንግስት ዝቅተኛ የመጠጥ ውኃ ባለባቸው አካባቢዎችን በማልማት ሕብረተሰቡ ከፍሎራይድ ነፃ ውሀ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልፀው ፕሮግራሙ በጊዜ የተገደበ በመሆኑ የጉድጓድ ቁፋሮው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል ።
በመጨረሻም በቢሮ ኅላፊ ማዕረግ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ በሚካሄድባቸው ቦታዎች/ሳይቶች ላይ በመገኘት የጥልቅ ውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ ለሚያካሄድ ለሀይድሮ ኮንስትራክሽን እና ኢንጂነሪንግ ስራ አስኪያጅ አቶ ቤሌማ ገመቹ የቦታ/ሳይት ርክክብ አካሄደዋል ።
Wolkite , Ethiopia
cerswimb10@gmail.com
+251113658301 