Skip to main content

በስልጤ ዞን ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዌራ ገረድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ።

ታህሳስ 19/2018 (ወልቂጤ)

በስልጤ ዞን አሊቾ ውሪሮ ወረዳ ወሻኖ ቀበሌ ከ21 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የዌራ ገረድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳዊት ሀይሉ እና በስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በመርሀ ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሀ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችን መፍታት የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት መሆኑን ገልፀዋል ።

በስልጤ ዞን ደረጃ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተደረገ ላለው ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ከፍ ያለ እውቅና የሰጡት አቶ ዳዊት የክልሉ መንግስት የውሃ ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን አቅም በፈቀደው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው በዞን ደረጃ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የዌራ ገረድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ዘይኔ አሁን ላይ በክልልና በዞን ደረጃ ፕሮጀክቶችን በተገቢው ለማጠናቀቅ ከተያዘ አቅጣጫ መነሻነት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

በዞን ደረጃ የመንግስትን ሀብት ከህብረተሰብ ተሳትፎ አቅም ጋር በማቀናጀት የመጠጥ ውሃ ሽፋኑን ለማሻሻል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ በአለም ገበያ፣ በቅበት፣ በሉቄ ፋቃ፣ በወራቤ ከተማና በሌሎች አከባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የዚሁ ርብርብ አካል መሆናቸውን አቶ ዘይኔ ተናግረዋል።

የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ መህዲያ ሀሰን በበኩላቸው ለዌራ ገረድ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ21 ሚሊየን በላይ ብር በዋን ዋሽ ፕሮግራም በማቺንግ ፈንድ መሸፈኑን ገልጸዋል።

በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የስልጤ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር፣ የስልጤ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ ክብርት ወ/ሮ ነይማ ሙኒር፤ የስልጤ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሙበራ ጀማል፣ የስልጤ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ዋና ሀላፊ አቶ ጨፋ ከድር፣ የክልሉ ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ  ምክትል ሀላፊና እና የመጣጥ ውሃ አቅርቦት ሳኒቴሽን ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሙላቱ ጡሞሮ እና ሌሎች የክልል የዞንና የወረዳው መንግስት የስራ ሀላፊዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል ።

Image